የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ በግማሸ ቀነሰ

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ በግማሸ ቀነሰ

የአማርኛ-ወሬዎች

በ2010 በጀት ዓመት ከአገራዊ የወጪ ንግድ አፈጻጸም 2 ነጥብ 83 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።ይህም ከዕቅዱ 54 በመቶ መሆኑ ተገልጿል።

በአፈጻጸሙ ከግብርናው ዘርፍ ለማግኘት ከታቀደው 3 ነጥብ 34 ቢሊዮን ዶላር ውሰጥ 2 ነጥብ 17 ቢሊዮን የተገኘ ሲሆን፣ ይህም 64 ነጥብ 9 በመቶ በማስገኘት ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል።

የማኑፋክቸሪንግ እና የማዕድን ዘርፍ በተከታታይ 458 ሚሊዮንና 122 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም ከእቅዳቸው 45 ነጥብ 9 በመቶ እና 15 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ በማሳካት የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የበጀት ዓመቱ የወጪ ንግድ አፈጻጻም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 2 ነጥብ 91 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የ71 ነጥብ 43 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ2 ነጥብ 43 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

የግብርናና እንስሳ ሀብት፣ የኢንዱስትሪና የነዳጅ፣የማዕድንና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴሮችና ሌሎች ተቋማት ድጋፍና ክትትል ከሚያደርጉት ውጭ በበጀት ዓመቱ የንግድ ሚንስቴር ድጋፍና ክትትል ከሚያደርግባቸው የግብርና ምርቶች ወጪ ንግድ አፈጻጸም 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ በአፈጻጸሙ ከ964 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት የተቻለ ሲሆን ይህም የእቅዱን 70 ነጥብ 9 በመቶ ድርሻ ይይዛል።

ለወጪ ንግድ አፈጻጸም መቀነስ የህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በሚፈለገው ደረጃ መግታት አለመቻል፣የምርት አቅርቦትና የጥራት ችግሮች መኖር፣ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስቶ የነበረው የጸጥታና ያለመረጋጋት ሁኔታዎች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የተሻለ ገቢ የሚያስገኙ የገበያ ዕድሎችን በመፈላለግና ትስስር በመፍጠር ረገድ የተሰራው ስራም አነስተኛ መሆኑ፣ የግብዓትና የአቅርቦት ችግሮች እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መዘግየት ለወጪ ንግድ አፈጻጸም መቀነስ ሌሎች በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው ሲል የንግድ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

(በኢ.ዜ.አ.)