የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአሜሪካ ለሚደረገው ዕርቀ ሰላም ሶስት ሊቃነ ጳጳሳት እንደምትልክ አስታወቀች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአሜሪካ ለሚደረገው ዕርቀ ሰላም ሶስት ሊቃነ ጳጳሳት እንደምትልክ አስታወቀች

የአማርኛ-ወሬዎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአሜሪካ ለሚደረገው ዕርቀ ሰላም ሶስት ሊቃነ ጳጳሳት እንደምትልክ የቤተክርስቲያኒቷ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አስታወቁ።

በ1984 ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን 4ኛው ፓትርያርክ መንበራቸውን ለቀው ከተወሰኑ አባቶች ጋር ከሃገር በመወጣታቸው በቤተ ክርስቲያኗ ለ26 ዓመታት ምዕመናን እያዘኑ በከፍተኛ የሰላም እጦት ውስጥ ማሳለፏን ቅዱስነታቸው ገልፀዋል።

የጠፋውን ሰላም ወደ ነበርበት እንዲመለስ ለማድረግም ቤተ ክርስቲያኗ ከ2003 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የተናገሩት።

በ2010 ዓመተ ምህረት ጥቅምት ወር የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔን ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት ከካህናትና ምእመናን የተወጣጣ የሰላም ኮሚቴ ያቀረበውን የዕርቅ ጥያቄ ተቀብሏል።

በዚህም መሰረት ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በአባቶች መካከል የሚካሄደውን የዕርቅ ሰላም ሂደት ፍፃሜ በማግኘት በውጭ የሚገኙ አባቶች ወደ ሃገር ውስጥ እንዲመለሱ ሶስት ሊቃነ ጳጳሳትን ወደ ስፍራው ያቀናሉ ነው ያሉት።

አሁን በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተጀመረውን ዕርቀ ሰላም ያለምንም መሰናከል ለውጤት ይበቃ ዘንድ ዕርቀ ሰላሙን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶሰ ፈቃድ ከሰጠው አካል በስተቀር መግለጫ መሰጠት ጠቃሚ አለመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ መንፈስ እየሄደችበት ያለው የህዝቡን ሰላምና እንድነት የማረጋገጥ ስራ ውጤትማ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።

ለዘመናት አንድነትና ቤተሰባዊነት የነበራቸው የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦችን ወደ ፍፃሜ ሰላም እንዲመጡ እየተከናውነ ያለው ጅማሮ ቤተ ክርስቲያኗ በእጁጉ የምትደግፈውና ለመጨረሻውም ግብ የበኩሏን አስተዋጽዖ የምታደረግ መሆኑ አስታውቃለች።

በመጨረሻም በቀጣይ ወቅቱንና ዘመኑን በዋጀ መልኩ መልካም አስተዳደርን በቤተክርስትያን ካለፈው በበለጠ ማስፈን እንዲቻል የቤተክርስትያኑን ችግሮች ሊፈታ ያስችላል በሚል በባለሙያዎች የተዘጋጀውን መሪ ዕቅድና ከአሁን በፊት የተጠኑ ጥናቶች በተግባር ማዋል እንዲቻል ጥናቶች ለ2011 ዓመተምህርት የጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ ዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡

(በኤፍ.ቢ.ሲ)