የአማርኛ-ወሬዎችየአማርኛ-ዜና

የአዲስ አበባ-ሞያሌ-ናይሮቢ-ሞምባሳ መንገድ ግንባታ ተጎበኘ

የአዲስ አበባ-ሞያሌ-ናይሮቢ-ሞምባሳ መንገድ ግንባታ ተጎበኘ

ከ13.5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ የሚገኘው የሞጆ-ሃዋሳ ዘመናዊ የፍትነት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስና በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተጎበኘ፡፡

 

የሞጆ-ሐዋሳ ዘመናዊ የፍጥነት መንገድ የአዲስ አበባ-ሞያሌ-ናይሮቢ-ሞምባሳ የመንገድ ኮሪደር አካል ነው፡፡

ይህ መንገድ ኮንትራት አንድ ሞጆ-መቂ 56.4 ኪ.ሜ ፣ ኮንትራት ሁለት መቂ-ዝዋይ 37 ኪ.ሜ ፣ ኮንትራት ሶስት ዝዋይ-አርሲነገሌ 57.1 ኪ.ሜ እና ኮንትራት አራት አርሲነገሌ-ሃዋሳ 52 ኪ.ሜ ተብሎ በአራት ኮንትራቶች በመከፈል ግንባታው እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ፣ የመንገዱ አጠቃላይ ርዝመትም 202.5 ኪ.ሜ ነው፡፡

መንግስት የሚከተለውንና ተግባራዊ እያደረገ ያለውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ መሰረት ባደረገና ለአካባቢውም እጅግ በጣም ትልቅ ውበት በሚሰጥ መልኩ የሚገነባው የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ እንደ አዲስ-አዳማ ዘመናዊ የፍጥነት መንገድ በሚታጠረው ዘመናዊ አጥር ተጠቃሚውን ያለስጋት በፍጥነት መጓዝ ያስችላል፡፡ በመሆኑም መንገዱ ከእግረኛና ከእንስሳ ነፃ በመሆን በመስመሩ ላይ ያለውን የአደጋ መጠንም በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ መንገዱ የሚታጠር በመሆኑ ከግራ ወደ ቀኝ የአካባቢው ነዋሪዎች መንገዱን ማቋረጥ የሚችሉባቸው ድልድዮች በአግባቡ ይገነባሉ፡፡ መንገዱ የፍጥነት መንገድ እንደመሆኑ መጠን ሌሎች መንገዶችን በሚያቋርጥበትና ወደ አካባቢው ከተሞች በሚገናኝበት ስፍራዎች ሁሉ ማሳለጫዎች እንዲኖሩት ተደርጎ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም በመንገዱ መሃል ላይ 9 ሜትር ስፋት ያለው የመንገድ አካፋይ የሚሰራለት ሲሆን ፣ ይህም የተቃራኒ አቅጣጫ ተሸከርካሪን ፍሰት በመለየት አደጋን ለማስወገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

መንገዱ አራት መኪኖችን በአንድ ጊዜ በግራና በቀኝ በኩል ለማስተናገድ በሚያስችል መልኩ እየተገነባ ያለ መንገድ ሲሆን ፣ በአንድ አቅጣጫ ሁለት መኪኖችን የሚያስተናግደው ይህ መንገድ እያንዳንዱ 3.65 ሜትር ስፋትና በ9 ሜትር ሜዲያን (የመንገድ አካፋይ) ያካተተ ሆኖ ከ1.75 ሜትር እስከ 2.25 ሜትር የመንገድ ትከሻ ስፋት የያዘ ነው፡፡

ይህ በአራት ኮንትራት ተከፍሎ ግንባታው የሚካሄደው የሞጆ-ሐዋሳ ዘመናዊ የፍጥነት መንገድ 32 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ፣ 90 ሜትር ስፋት ያለው የመንገድ ወሰን ማስከበር ክልልን ያካተተ ነው፡፡ ይህም በቀጣይ ለሚኖረው የማስፋፋት ስራ በቂ ቦታ እንዲኖር የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር ፣ በዚህ ቦታ ላይ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መሰረት በማድረግ ችግኝ በመትከል አካባቢውን ለማስዋብ ጥሩ የሆነ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

የመንገዱ መገንባት አስፈላጊ የሆነው ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ከፍተኛ ድርሻ ያለውና በመስመሩ ላይ የሚገኙትን ወረዳዎች ፣ ከተሞችና የእርሻና የኢንዱስትሪ ቦታዎችን እንዲሁም የቱሪስት መስህብ የሆኑ ቦታዎችን ለማገናኘትና ከዚህም ባሻገር ከአዲስ አበባ-ሞያሌ-ናይሮቢ-ሞምባሳ ያለውን የኢትዮጵያን የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሳለጥ ለማስቻል ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር የሞጆ-ሐዋሳ መንገድ 10,000 ኪ.ሜ የሚሸፍነው የታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ኮሪደር የኢጅብት ካይሮ-ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ትራንስ አፍሪካን ሃይዌይ አካል በመሆኑ የአገራችንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መንገድ ነው፡፡

(በፌደራል መሰረተ ልማት ክላስተር)