አዲስ አበባ ለምን ደመቀች? ዶክተር ብርሀኑስ ይህ ይገባዋል??

አዲስ አበባ ለምን ደመቀች? ዶክተር ብርሀኑስ ይህ ይገባዋል??
አዲስ አበባ ለምን ደመቀች? ዶክተር ብርሀኑስ ይህ ይገባዋል??

በመላኩ ብርሀኑ – ከሰኞ ጀምሮ ዛሬ ድረስ አዲስ አበባ በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራ ደምቃለች። በትራፊክ መብራት ላይ መነፅርና ቦሎ መለጠፊያ ያዞሩ የነበሩ ሁላ አሁን ዘንግ ላይ የታሰረ ባንዲራ መሸጥ ጀምረዋል።ታክሲዎችም ይህንኑ ባንዲራ ሰቅለው ነው ሲዞሩ የሚታዩት።

የከተማዋ መንገዶችና የግቢ በራፎች ሁሉ ህዝብ በተከለው ኮከብ አልባ ባንዲራ ማሸብረቃቸውን ስታዘብ በፈረንሳይኛ የተሰራ አንድ ዶክመንታሪ ላይ ያየሁትን ትዕይንት አስታወሰኝ።

ፋሽስቱ የጣሊያን ወራሪ ድል ተመትቶ ከኢትዮጲያ መውጣቱን ተከትሎ አፄ ሃይለስላሴ ከስደት ተመልሰው አዲስ አበባ ሲደርሱ ህዝቡ ያደረገላቸው አቀባበል የሞቀ ነበር። በየሰፈሩ ባንዲራ ተተክሎ ህዝብ በሰልፍ ወጥቶ ሲጨፍርና ሲፎክር አይቻለሁ።

ነገ አርበኞች ግንቦት ሰባት ግንባር ከመሪው ዶክተር ብርሀኑ ነጋ ጋር አዲስ አበባ ይገባል። የከተማዋ በኮከብ አልባ ሰንደቅ አላማ ማሸብረቅ አላማውም ይኸው ነው።

እንደምገምተው አዲስ አበባ በድምጿ የመረጠችውን ነገር ግን “የህዝብ ድምፅ ተጭበርብሯል” በማለት ወንበሩን ላለመረከብ አቋም ይዞ የቆየውን ኋላም የታሰረውንና በመጨረሻም ተሰድዶ ይህንን ስርአት በትጥቅ ትግል ለመፋለም በረሀ የገባውን በመጨረሻም የአሸባሪነት ካባ የተደረበለትን ዛሬ ግን ነገር አለም ተቀያይሮ ዳግም ወደሰላማዊ ትግል ለመቀላቀል አዲስ አበባ የሚገባውን “ከንቲባዋን” ሞቅ አድርጋ ለመቀበል ተዘጋጅታለች። ለዚህ ነው የደመቀችው።

ግን አርበኞችንም ግንቦት ሰባትንም ለጊዜው እንተዋቸውና “ዶክተር ብርሀኑ ነጋ እውን ይህ የጀግና ክብርና አቀባበል ለምን ይገባዋል?” ብለን እንጠይቅ።

አዲስ አበባ ለምን ደመቀች? ዶክተር ብርሀኑስ ይህ ይገባዋል??
አዲስ አበባ ለምን ደመቀች? ዶክተር ብርሀኑስ ይህ ይገባዋል?? Photo- Petros Ashenafi Kebede

የግሌ እምነትና አስተያየት ይህ ነው።

አበው “ወርቅ በእሳት ሰው በመከራ እና ክፉ ቀን ይፈተናል” ይላሉ። እሳቱን ያለፈ “ትክክለኛ ወርቅ”፣ መከራና ክፉ ቀንንም በድል ያለፈ “እውነተኛ ሰው” ተብለው ይጠራሉ።

ዶክተር ብርሀኑ ነጋ በመልካም ዘመን የታየ ፖለቲከኛ ሳይሆን በክፉ ቀን ብቅ ብሎ ወደበለጠ ክፉ ቀን የተገፋ ፣ ያንንም ተፈትኖበትና ኖሮበት በአንድ አቋሙ ፀንቶ ዛሬ ድረስ የኖረ እውነተኛ ሰው ነው።

በህይወቴ ይህንን ሰው አጠገቤ ቆሞ ያየሁት በ1992 ዓም ነው።ከዚያ በፊት አላውቀውም። ከዚያ በኋላም በአካል የተገናኘንበት አጋጣሚ አልነበረም።

አዲስ አበባ ለምን ደመቀች? ዶክተር ብርሀኑስ ይህ ይገባዋል??
አዲስ አበባ ለምን ደመቀች? ዶክተር ብርሀኑስ ይህ ይገባዋል??

የዛሬን አያድርገውና የጋዜጠኝነት ስልጠና በሽ በነበረበት በዚያ ወቅት የአለም ባንክ “investigative journalisn and corruption reporting” በሚል ርዕስ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለጋዜጠኞች በሰጠው ወርክሾፕ ላይ ተካፋይ ነበርኩ።

በወርክሾፑ አሰልጣኝ ከነበሩት ታዋቂዎቹ ኢኮኖሚስቶች እነ ፒተር ኪብሪቲ እና ስሙን ለጊዜው የዘነጋሁት የ Curbing corruption መፅሀፍ ደራሲ ጋ ዶክተር ብርሀኑ ነጋ አንዱ አሰልጣኝ ነበር።የርሱ ርዕስ economic reporting ነበር።

መቼም ይህ ሰው ያለው ዕውቀት ለሰው አይነገርም። እንኳን እኛ “ኔፓዎቹ” ቀርተን የአለም ባንክ ወኪል የነበሩት ምሁራን ፈረንጆች ሁሉ አፋቸውን ከፍተው ሲያደምጡት ፣ ጭራሽ እኛ ዝም ብለን እነሱ ሰልጣኞች ሲሆኑ ሳይ ሰውየውን የበለጠ የማወቅ ጉጉት አደረብኝ። በዚያን ቀን ስለኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እና ስለኢህአዲግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተናገረውን ነገር እስከዛሬ አልዘነጋውም።በአጭር ቃል መፅሀፍ የሚወጣው ሃረግ።

“The economic policy of EPRDF is a shame like sex between families”

በጣም ነበር የገረመኝም ግራ የገባኝም። ይህ በርግጥ ከአእምሮ የማይወጣ ከባድ አገላለፅ ነው። መልሱን የተነተነበት መንገድ በጊዜው ባይገለፅልኝም የፖሊሲው ስህተት ምን እንደሆነ እንዲያብራራልኝ አንድ ሁለት ጥያቄም ጠይቄው ነበር።

በመጨረሻ የፒተር ኬ· ን “ብራውን ኤንቨሎፕ” (ጋዜጠኞች ቡጬ የምንላትን) በልቤ ፣ የዶክተር ብርሃኑን sex between families በአእምሮዬ ይዤ ከስልጠናው ወጣሁ።

የዚህን ሰው ድፍረት አለማድነቅ ከባድ ነበር። በዚያ ኢህአዴግ “እንደግል አዳኝ” ይቆጠርበት በነበረበት ዘመን በአላዋቂዎች ወይም እያወቁ ተንኮል በሸረቡ ሰዎች የተተበተበው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የውሸት አሀዞች ከማምረት ውጪ ሀገሪቱን የትም እንደማያደርሳት ቀድሞ መተንበይ ብቻ ሳይሆን በአደባባይ “አስተካክሉ ፣ ልክ አይደለም” ብሎ መቃወም በርግጥም በራስ መተማመንን እና የአቋም ሰው መሆንን ይጠይቃል።

ብርሀኑ ከዚያ በኋላ በሰማሁት ማንነቱ ከሚያስተምርበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደሞዙን አንድም ቀን ተቀብሎ የማያውቅ ፣ለተቸገሩ ተማሪዎች መርጃ የሚያውል ፣ በጣም ተወዳጅና ለህሊናው ብቻ ያደረ ምሁር መሆኑን ሳውቅ የበለጠ አከበርኩት።

እዚህ ላይ እውነተኛ ሰው የሚፈተንበትን “የግል ጥቅምን ትቶ ለሌሎች የመኖርና የማሰብን” ከባድ ፈተና ብርሀኑ መወጣት እንደቻለ በሰማሁት ብቻ ያለአስረጂ አምኜ ነበር።

ከሶስት አመታት በኋላ ያ ሰው ቅንጅትን መስርቶ ብቻውን የሚቃወመውን ፓርቲ ከመሰሎቹ ጋር ተደራጅቶ ሲገዳደረው ሳይ በፖለቲካው መድረክ የሚኖረውን አሸናፊነት አልተጠራጠርኩም። ፀብ አይንቅም የሚባለው ኢህአዴግ አለመጠን ራሱን አሳብጦ አይቶና ህዝቡን for granted እንደገዛው ተማምኖ ምርጫ 97 ላይ ከዚህ ትንታግ ሰው ጋ ሊወዳደር ሚዲያ ላይ ቢወጣ ዝም ብሎ ከመቅጨልጨል በቀር ውስጡ good for nothing የሆነ ባዶ ቅል እንደነበር ተጋለጠበት። ያው ምርጫውም እንዳየነው ሆነ። መለስ ዜናዊ ጥሩ አድርጎ እንደገለፀው “ዝረራ!!”

ከዚያ በኋላ የነበረውን political sabotage እና conspiracy እንተወው። ብርሀኑ ነጋ ግን ለምን የሁልጊዜም አሸናፊ እንደሆነ እናውራ።

አቋሙ አይናወጥም።ሃገርና ህዝብ ከራሱ ! እደግመዋለሁ ከራሱ ! የሚያስቀድማቸው አጀንዳዎቹ ናቸው። ለዚህ ደሞ ማረጋገጫ አለ።

ብርሀኑ ምንም ችግር የለበትም። እንኳን ኢትዮጲያ ውስጥ ቀርቶ ሌላ ሀገርም አንቀባርሮ አዘንጦ ሊያኖረው የሚችል ገቢ የሚያገኝበት እውቀት ባለቤት ነው። ይህን ኢትዮጲያ ውስጥ አስተምሮም አሜሪካ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አስተምሮም ከፍተኛ ተከፋይ ሆኖ አይተነዋል።

ደሞዙን የማይቀበል እና ለደሞዝ የማይሰራ ሰው ነው። እንግዲህ

አዲስ አበባ ለምን ደመቀች? ዶክተር ብርሀኑስ ይህ ይገባዋል??
አዲስ አበባ ለምን ደመቀች? ዶክተር ብርሀኑስ ይህ ይገባዋል??

የሀብታም ልጅ ስለሆነ የገንዘብ ችግር ስለሌለበት የሚል ምክንያት ቢነሳ ያስኬድ ይሆናል። በርግጠኝነት ግን ገንዘብም ምቾትም ማጣት ለማንም ደግ የሚባል ሰው ምርጫ ሆኖ አያውቅም ። እየቻሉ ምቾት ማጣት የአላማ ሰው መሆንን ይፈልጋል።

ብርሀኑ አላማ አለው። ይህንን ለማሳካት ደግሞ ሪስክ ይጋፈጣል። የአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የገባው የፖለቲካው ችግር ገብቶት እንጂ ስሜት ወይም ወኔ ወዝውዞት አይደለም። “ከ እስከ” ድረስ አዋቂ መሆኑን በምርጫ 97 ጊዜ አሳይቶናል። በምክንያት መቃወም ፣ በማስረጃ መተቸት፣ በመፍትሄ መደራደር (በተለይ with honesty ) እንዴት እንደሆነ አሳይቶናል። በዚህ ሳቢያ እሱን አይተን ተስፋ ሰንቀን፣ከእንቅልፋችን ነቅተን ቅንጅትን መርጠናል። ምርጫ 97 ብርሀኑ ባይኖርበት ኖሮ ዘላለም የደመቀ ታሪክ ይዞ አናየውም ነበር።

ብርሀኑ “በይሁን በቃ” (compromisation) አያምንም። ምርጫ 97 ላይ ቅንጅትን ይዞ አሸነፈ። ኢህአዴግ ከባድ ወጥመድና ተንኮል ተብትቦ “ፓርላማ ግባ ከተማዋን ተረከብ” አለው።

ብዙዎች “ቢገባ ቢረከብ” ፣ “አትግባ አትረከብ” በሚል ድጋፍና ተቃውሞ ልባቸው የሚዋልልበት ፓርላማ መግባትና አዲስ አበባን መረከብ ለርሱ የአሸናፊነት ምርጫ አልነበረም። “የህዝብ ድምፅ ተጭበርብሯል፣ ፍትህ ተጥሷል ፣ፓርቲው እውነተኛ ጭንብሉ ተገልጧል ፣ ሌላ መሰረታዊ የትግል ምክንያት ተፈጥሯል” ብሎ የተዘጋጀለትን ትሪ ገልብጦ ተነስቷል። ግን ለህዝብ አንድ እድል ሰጥቷል። አስተያየት ጠይቋል። ህዝቡም አቋሙን ደግፎታል። እሱም በመስመሩ ፀንቷል። ይሁን በቃ አላለም።

ብርሀኑ ኢህአዴግን የምንጊዜም ባላንጣው ሲያደርግ እንደአብዛኞቻችን ሌላ ምርጫ አጥቶ አይደለም። ዝም ቢልና ቢኖር አንድም ቀን ጥርሱ ሳይከደን መኖር ይችላል። ግን ከራሱና ከቤተሰቡ ሰላምና ጥቅም በላቀ የሀገሩ እና የህዝቡ ጉዳይ ፋታ ስለነሳው ህይወትን በሚጠይቅ ድፍረት በውቅያኖስ ካደፈጠው iceberg ጋ መጋጨትን መርጧል። በዚህ ሳቢያ ታስሯል።አሸባሪ ተብሎም ተፈርዶበታል። ቤተሰቦቹም መኖሪያ ቢዝነሳቸው ዶግ እስኪሆን ፍዳ አይተዋል።

ሀገር ለቆ ሲወጣ ሁለት ነገር መርጦ ነው። እንዲህ በጭቆና ውስጥ የሚኖር ህዝብና አገር ዜጋ ከመሆን ወይ ታግሎ መጣል ወይ ታግሎ መሞት።

ምሁር፣ከእስክሪፕቶና አንደበት የዘለለ መሳሪያ የሌለው ለዚያውም ተንደላቅቆ ያደገ ሰው ክላሽ ይዞ በረሀ ዘለቀ።

ከላይ የፃፍኩትን ማንነት ተውትና የኔ ዋናው አድናቆት እዚህ ላይ ነው። (ምናልባት ፈሪ ስለሆንኩ) ጦርነትን እንደትግል አማራጭ ከማይቀበሉት ሰዎች አንዱ ብሆንም በብርሀኑ አቋም መደነቄን ብሸሽግ ቀሽም ነኝ።

እስኪ ለነፃነት እና ለፍትህ እዚህ ርቀት ድረስ የተጓዘ ሰው ፈልጉ። ይህ እኮ በ1967 ህወሃት ነፍጥ አንግቦ ደደቢት ሲገባ የተወደሰለት አይነት በእውነተኛው የታሪክ መዝገብ የሚሰፍር “እምቢ ባይነት” አንድ ጀብድ ነው። ለዚያውም ብርሀኑ ብሄርተኛ ድርጅት ሳይሆን ኢትዮጲያዊ ቅርፅና ባህሪ ያለው ፓርቲ እየመራ ነው በረሀ የገባው። ለምን ብሎ? ለማን ብሎ?

እንደማንም ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ቂጡን እየወዘወዘ መግለጫ መስጠት ሲችል? ፣ እንደማንም ከኢህአዴግ ለፓርቲ የሚበጀተው በጀት ላይ “አነሰ ጨምሩ” እያለ ተከራክሮ መብላት ሲችል?እንደማንም ቃል አሰማምሮ ዲፕሎማቲኮችን እየተጠጋ እርጥባን ማግኘት ሲችል?

ብርሀኑ ለኢህአዴግ ግንቦት ሰባትን ያህል በስሙ አስበርጋጊ ፓርቲ ፈጥሮበት እስከመጨረሻው አማራጭ ሲታገለው ብቸኛ አጀንዳው አንድነት፣ዴሞክራሲና ነፃነት ነበር። ለኛ ሲል ካልሆነ ለማንም ሲል ራሱን ለሞት አፍ አሳልፎ አልሰጠም። ቢጠጋቸው ቢሊየነር ሊያደርጉት ሲችሉ፣ ራሴን እችላለሁ ቢል እንኳን ዲታ መሆን ሲችል እርሱ ከ ቢች ዳር ቤት ይልቅ የበረሀ አሸዋ ምሽግ መርጧል።

ብርሀኑ በዶክተር አብይ አማካኝነት የሚፈልገው ለውጥ ሲመጣ ምን አለ?። “የምንሻው ለውጥ ነው። ለውጡን የግድ እኛ እናምጣው አንልም። ለውጥ ያመጣውን ሁሉ እንደግፋለን። ስለዚህ ለውጥ ላለማደናቀፍና በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ለመሳተፍ የትጥቅ ትግል አቁመናል።”

ካላስ!!

ምን ትፈልጋለህ !። የራስ ወዳድነትና “የእኔ ብቻ” ፖለቲካ በዚህ ሰው አፈር ሲገባ አየህልኝ?። ፖለቲካው ይቆየንና እስኪ ማነው በዚህ ፅናት ውስጥ ራሱን ፈትኖ “ሆኖ መገኘት” የሚችል? አላየሁም!!

ስለዚህ ብርሀኑ ይህ የጀግና አቀባበል ይገባዋል ብቻ ሳይሆን ያንሰዋል። የአላማ ሰው ነው። ሰው ሲጠፋ ለሀገር የተገኘ አንድ ሰው። ከዚህ በኋላም ለኢህአዴግ ብቸኛ ተገዳዳሪው እሱ ነው።

ይህን ሰው ከዚህ በላይ አልገልፀውም። አለማድነቅ ይከብደኛል። የእሱን ፅናት አለመመኘት ይከብደኛል።

ብቻ “እንኳን ደህና መጣህ! ላንተ የአዲስ አበባ ድምቀትና አቀባበል ይገባሃል!! ” እለዋለሁ።

kudos ! Prof. Berhanu Nega