በኦሮሚያ ክልል ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል

በኦሮሚያ ክልል ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል

የአማርኛ-ወሬዎች

በኦሮሚያ ክልል በ2011 በጀት ዓመት ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር መታደቁ ተገለፀ። ይህ የተገለፀውም በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የኦሮሚያ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እና የክልሉ ከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አወሉ አብዲን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ የስራ ሀላፊዎች በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የክልሉ ከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በመድረኩ ላይ እንዳስታወቀው፥ በ2011 በጀት ዓመት የስራ ድል ለሚፈጠርላቸው ወጣቶች 3 ነጥብ 283 ቢሊየን ብር ብድር ተዘጋጅቷል።

በዚህም 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ወጣቶችን በ90 ሺህ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለማደራጀት መታቀዱን ነው ኤጀንሲው ያስታወቀው።

የስራ እድል ከሚፈጠርላቸው ወጣቶች ውስጥም 64 ሺህ የሚሆኑት ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ተመርቀው የወጡ ናቸው።

በክልሉ ስራ ይፈጠርላቸዋል ለተባለው ወጣቶችም 52 ሺህ 205 ሄክታር የከተማ እና የገጠር መሬት መዘጋጀቱንም ኤጀንሲው አስታውቋል።

እንዲሁም 4 ሺህ 648 አዳዲስ የመስሪያ ሼዶች የሚሰሩ መሆኑም ተገልጿል።

የክልሉ ከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አወሉ አብዲ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፥ የ11 ቢሊየን ብር የገበያ ትስስር በመፍጠር ማህበራቱ እስከ 9 ቢሊየን ብር እንዲቆጥቡ ይሰራል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የ2010 በጀት ዓመት ክንውን ሪፖርትም የቀረበ ሲሆን፥ በዚህ በጀት ዓመት 988 ሺህ ስራ አጦች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉ ተገልጿል።

ከእነዚህም ውስጥ 35 ሺህ የሚሆኑት ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ተመርቀው የወጡ ናቸው።

ለዚህም 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በብደር የተሰጠ ሲሆን፥ 51 ሺህ ሄክክታር የከተማ እና የገጠር መሬት ለስራ አጦች እንዲከፋፈል መደረጉ ነው የተነገረው።

በጉባኤው ላይ በስራ እድል ፈጠራ ጥሪ ተሳትፎ ያደረጉ ሴክተሮች፣ ከተሞች፣ ዞኖች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ባለሃብቶች እውቅና እና ሽልማት ከፕሬዚዳንቱ ተበርክቶላቸዋል።